Sunday, April 1, 2012

Kingdom dynamics


መሲሐዊ  ምልከታ በ ዘፍ 41
አብርሃም  ጌታቸው

ምስጋና
ይህንን  ጽሁፍ  እንዳዘጋጅ  ምክንያት  የሆነኝ  የዕብራይስጥ  ቋንቋ  አስተማሪዬን  ዶ/ር ቨርን  ስታይነርን  ላመሰግን  እወዳለሁ።

አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤«በእግዚአብሔር (ያህዌ) ርዳታ ወንድ ልጅ2 አገኘሁ» አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች።
አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር።

አዳም እንደ ገና ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምትክ ሰጠኝ ስትል ስሙን ሴት  ብላ ጠራችው።
ዘፍ 41-2 እና 25-26

            አብዛኛውን ጊዜ ድነትን አስመልክቶ በዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ውስጥ ሲጠቀስ የምሰማው ምዕ 315 ላይ ያለው በስነ-መለኮት ቅድመ ወንጌል ወይንም የመጀመሪያው ወንጌል (ፕሮቶኢዋንጌሊዎንተብሎ የሚጠራው ጥቅስ ነው። ጥቅሱ ይህንን መጠሪያ ያገኘው እግዚአብሔር ለመጀመሪያዎቹ ቤተሰቦች ብሎም ለዓለም ህዝብ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የድነትን ተስፋ የሰጠበት ክፍል በመሆኑ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ቀጣይ ታሪክ የተለመውም ይህ ጥቅስ ነው። ነገር ግን በዘፍ ላይ የምናገኘው የመጀመሪያው ቤተሰብ ታሪክ በተለይም ሔዋን ስለልጆችዋ የነበራትን እምነትና ያንንም ያንጸባረቀችበት መንገድ ከዘፍ 315 በተጨማሪ ገና ከጠዋቱ ድነት በመጽሃፍ  ቅዱስ ዋነኛ ትምህርት መሆኑን ጠቋሚ ነው። እኔም በዚህ ጽሁፍ ድነትን የሚያስገኘው የሴቲቱ ዘር መወለድ ለመጀመሪያው ቤተሰብ አልፎ ተርፎም ለሰው ልጆች ምን ያህል ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ሔዋን ለልጆችዋ በሰጠቻቸው ስሞች አማካይነት ለማሳየት እሞክራለሁ።
            አዳምና ሔዋን ከዔድን ገነት ከተባረሩ በኋላ ሔዋን እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል በሚገባ ያስተዋለች ትመስላለች። በተለይም «እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል» ተብሎ ስለዘርዋ የተነገረውን የተስፋ ቃል። እግዚአብሔር ይህንን ቃል በቀጥታ የተናገረው ለእባቡ ቢሆንም ጉባዔው አዳምንና ሔዋንን ያካተተ ስለነበር ፍርዱ ምን እንደሚመስል ያውቃሉ። እግዚአብሔር በእባቡ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ለእነርሱ የአርነት ተስፋ የሚሰጥ ስለነበር ቃሉ መጽናናት እንዳስገኘላቸው ጥርጥር የለውም። በእባቡና በሴቲቷ ዘር መካከል በሚኖረው ቀጣይ ትግል እባቡ የሴቲቱን ዘር እግር ሊቀጠቅጥ ቢችልም ድል ነሺው ግን የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥ የተነገረለት የሴቲቱ ዘር ነው።
            ሔዋን ሃሳብዋ እንዲበላሽና እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል እንድትተላለፍ ያደረጋት የእባቡ የተንኮል ስራ መሆኑን አላጣችውም። ከእንግዲህ ወዲያ እባቡ ዳግመኛ ማንንም እንዳያስት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል የሚያደርግላትን ዘር ትናፍቃለች። ለዚህም ይመስላል የመጀመሪያ ልጅዋን ቃየንን ስትወልድ «በእግዚአብሔር እርዳታ  ሰው (በዕብራይስጥ ኢሽአገኘሁ» ያለችው።3 የአማርኛ ቅዱሳት መጻህፍት «ኢሽ» የሚለውን «ወንድ ልጅ» በማለት ተርጉመውታል። የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳንም ሆነ የሰብዓ ሊቃናት የግሪክ ትርጉም ከ«ወንድ ልጅ» ይልቅ «ሰው» የሚል ትርጉም ሊሰጡ የሚችሉ ቃላቶችን ነው የተጠቀሙት። የአማርኛ ቅዱሳት መጻሕፍት ለምን «ወንድ ልጅ» የሚለውን መጠሪያ መጠቀም እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም። ወንድ ልጅ ሰው እንደሆነ አላጣሁትም። ነገር ግን ሔዋን እግዚአብሔር ሰው ሰጠኝ ካለች በዚያ ውስጥ ማስተላለፍ የፈለገችው መልዕክት አለ። ያም መልዕክት እባቡን የሚቀጠቅጥ በሌላ አገላለጽ ድነትን የሚያመጣ ሰው (ዘርሰጠኝ ማለትዋ ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ ሔዋን በቃየን መወለድ እግዚአብሔር የሰጠው የአርነት ተስፋ እውን እንደሚሆን ያመነች ትመስላለች።
            ቃየን እናቱ ተስፋ ያደረገችበት ዘርዋ ቢሆንም እግዚአብሔር አልመረጠውም። እግዚአብሔር ካልመረጠው ደግሞ እግዚአብሔር የወደደውን መምረጥ የሚችል አምላክ በመሆኑ ሔዋን ከርሱ ሃሳብ ጋር መስማማት እንጂ ማመጽ  አይኖርባትም። እግዚአብሔር ለምን አንደኛውን መርጦ ሌላኛውን እንደማይመርጥ እንዲያስረዳ አይገደድም። እርሱ ሉዓላዊ አምላክ ነው። ለማንም መልስ ወይንም ማብራሪያ የመስጠት ግዴታም የለበትም። ሆኖም ግን ሰዎች አሳቡን አውቀው በዚያ ውስጥ ያለውን በረከት እንዲካፈሉ በወደደው መንገድ ዕቅዱን ይገልጥላቸዋል።
            እግዚአብሔር ከቃየን ይልቅ አቤልን እንደመረጠ ገና ከመጀመሪያው ፍንጭ የሚሰጠን ዘፍ 4ነው። ቃየን በኩር ስለሆነ ሔዋንም ተስፋ ስለጣለችበት ቅድሚያ ሊጠቀስ ይገባው ነበር። የዘፍጥረት ተራኪ/ጸሃፊ ግን በቅድሚያ የጠቀሰው የታናሹን የአቤልን ሙያ ነው። ለጠቅ ብለን ቁጥር ን ስናነብ እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመልክቶ ቃየንና መስዋዕቱን ጉዳዬ አለማለቱ እግዚአብሔር ቃየንን እንዳልመረጠው ሌላኛው ማስረጃ ነው። አንዳንድ  የመጽሃፍ ቅዱስ አጥኚዎች ሔዋን ደግማ ስትወልድ እንጂ ስትጸንስ አለመጠቀሱን እንደምክንያት በማቅረብ ቃየንና አቤል እንደ ዔሳውና ያዕቆብ መንታ ሳይሆኑ አይቀሩም ይላሉ። ግራም ነፈሠ ቀኝ ቁም ነገሩ ያለው የዘፍጥረት ጸሃፊ ታላቁ እያለ ታናሹ መመረጡን አንባቢው እንዲያስተውል መፈለጉ ላይ ነው። ታዲያ ሔዋን ቃየን ባለመመረጡ ከሰረች  ማለት ነውንእግዚአብሔር የተናገረለት ዘር ቃየን ይሁን አቤል ከርሷ ዘሮች አንዱ እስከሆነ ድረስ የጠበቀችው ባይሆን  እግዚአብሔርን ትከሰዋለችንየርሱንስ መንገድና ምርጫ አልቀበልም ትላለችን?
            ሔዋን የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ የሚፈጸመው በርሷ ዘር አማካይነት እንደሆነ ብትረዳም ተስፋ ያደረገችው  ቃየን ግን ያ ዘር አልነበረም። ትክክለኛ መረዳት ኖሯት ትክክለኛ ያልሆነ ሰውን ተስፋ ማድረግዋ ከርሷ በኋላ ለመጡት  ዘሮችዋ እንደ ምሳሌ ያደርጋታል። ሕያዋኑ የሔዋን ልጆች አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው አላጡትም። ስህተታቸው ያንን አዳኝ በሌሎች ነገሮች እና ሰዎች ውስጥ መፈለጋቸው ነው። ለዚህ ዓይነቱ ስህተት ሔዋን የመጀመሪያዋ እንጂ የመጨረሻዋ አትሆንም። ይስሃቅ ከያዕቆብ ይልቅ ዔሳውን ሊባርክ ተዘጋጅቶ አልነበረምንእንዲያውም ዔሳውን የባረከ ነው የመሰለው (ዘፍ 2733)። እሴይስ ቢሆን እግዚአብሔር ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉስ እንዲሆን ይመርጠዋል ብሎ መች አሰበ (1 ሳሙ 1610-13)? በርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰው ተስፋ ያደረጋቸው ሳይሆን በሰው ግምት ያልተሰጣቸው ሰዎች እግዚአብሔር መርጧቸው የትድግና ስራ ሲሰሩ ይታያሉ።
            የአቤልን ስም ትርጉም በርግጠኝነት መናገር አይቻለኝም። ስሙንም እንዴት እንዳገኘው አልተጠቀሰም። ስሙን የሰጠችው ሔዋን ነበረች ብለን እንገምትና ምን እያሰበች አቤል እንዳለችው ብትነግረን ጥሩ ነበር። አቤል ማለት  እስትንፋስ ወይንም ትነት የሚል ትርጉም ከሚሰጠው «ሄቬል» ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስላል።4 ለነገሩ የአቤልም ስም በዕብራይስጥ «ሄቤል/ሃቬል» ነው።5 እንዲያ ከሆነ አቤል እንደ ትነት ከዕይታ የሚጠፋ ከንቱ የሚሆን ማለት ነው።6 እንግዲህ ሔዋን አቤልን ከንቱ ካለችው ለምን የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ህይወቷ ከእግዚአብሔር ውጪ በከንቱነት መሞላቱን ለመግለጽ ፈልጋ ከሆነ ተሳስታለች ማለት አልችልም። ህይወት ከእግዚአብሔር ውጪ እንደገመተችው አልሆነላትም። እግዚአብሔር ክፉና ደግ ያለውን እርሷም ተከትላ ክፉና ደግ ከማለት ይልቅ ክፉ ምን እንደሆነ ደጉም ምን እንደሚመስል ያለ እግዚአብሔር እርዳታ በራስዋ ለመወሰን ስለመረጠች የመንገድዋን ፍሬ እየበላች ነው። የመጽሃፈ መክብብ ሰባኪ ህይወት ከእግዚአብሔር ውጪ «ከንቱ፣ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ» እንደሆነ ሲገልጽ በዕብራይስጥ «የሃቬልም ሃቬል የሃቬልም ሃቬል ሁሉም ነገር ሃቬል» ነው  ይላል። ሃቬል አቤል ከንቱ!
            የአቤል ህይወት ግን ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ምንም እንኳ በወንድሙ ቢገደልም በመረጠው የጽድቅ ህይወትና  ለእግዚአብሔር ባቀረበው መስዋዕት የእምነት ምሳሌ ሆኗል። የዕብራውያን ጸሃፊም በእምነታቸው ስለተመሰከረላቸው  ሰዎች በተናገረበት በ11ኛው ምዕራፍ በመጀመሪያ የጠቀሰው አቤልን ነው። አቤል ዋጋ ቢያስከፍለውም ከስሙ በላይ  የሆነ የጽድቅ ህይወት ኖሯል።
            ሔዋን ቃየንን አስመልክቶ የነበራት እምነት የተሳሳተ መሆኑን፤ ባንጻሩ እግዚአብሔር አቤልን መምረጡን የተገነዘበችው መቼ እንደሆነ መናገር ባልችልም በስተመጨረሻ ወደትክክለኛ መረዳት ላይ ደርሳለች ብዬ አምናለሁ። እንደምገምተው እግዚአብሔር አቤልንና መስዋዕቱን ተቀብሎ ቃየንንና መስዋዕቱን ሲንቅ አይታለች። ቃየንም እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት ህይወት በንስሃ ከመመለስ ይልቅ ወንድሙን ገድሎ ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል መምረጡንም ተመልክታለች። በስተመጨረሻ እግዚአብሄር የፈለገው እርሷ ከግምት ውስጥ ያላስገባችውን ታናሹን ልጇን አቤልን መሆኑን ስታውቅ እርሱን ለማዳን ጥረት አለማድረጓ ጸጸት ውስጥ ከቷትም ሊሆን ይችላል።7
            እግዚአብሔር ቸር አምላክ ስለሆነ እንደገና ዕድል ይሰጣል። ሁለቱንም ልጆችዋን ካጣች በኋላ ለሔዋን ሌላ ዘር እንድትተካ ዕድል ሰጣት። ይህ ዘር እግዚአብሔር መርጦት የነበረው የአቤል ምትክ ነው። ሔዋን ይህንን ስለተገነዘበች «ሴት» የሚለውን ስም ለምን እንደሰጠችው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦

ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምትክ ሰጠኝ

            ሴት የስሙ ትርጉሙ ምን እንደሆነ በግልጽ መናገር አይቻልም። አዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ቅ የገጹ ጠርዝ ላይ «ሴት ማለት ሰጠ ማለት ሳይሆን አይቀርም» ይላል።8 ሔዋን «ሴት» የሚለውን ስም ለዚህኛው ልጅዋ የሰጠችው  «እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ» ስላለች ነው። «ሰጠኝ» ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ «ሺት» አስቀመጠ፣ ጫነ  ወይንም ሾመ የሚል ትርጉም ነው ያለው።9 ስለዚህ ሔዋን የአቤል ምትክ የሆነላትን ልጅዋን «ሴት» ያለችው እግዚአብሔር ሌላ ዘር እንዳስቀመጠላት ወይንም እንደሾመላት ስላመነች ነው። ለዚህም ይመስላል ያመሳከርኋቸው የእንግሊዝኛ ቅዱሳት መጻህፍት «እግዚአብሔር ሾመልኝ» የሚል ትርጉም የመረጡት።10 የሰብዓ ሊቃናት የግሪክ ትርጉም የሔዋንን አባባል «እግዚአብሔር ለእኔ ሌላ ዘርን አስነሳልኝ» ይለዋል።11
            የሴት መወለድ አንድ ልጅ ሲሞት በሌላኛው እንደሚተካው ዓይነት አልነበረም። በባህላችን አንዳንድ ቤተሰቦች ልጅ ሲሞትባቸው በቀጣይነት የሚወልዱትን ልጅ ካሳ፣ ተካልኝ፣ ምትኩ የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ስሞችን  ሲሰጡ ይስተዋላሉ። ምናልባትም እግዚአብሔር በሌላ ልጅ ካሰን ለማለት ተፈልጎ ይሆናል። ዳሩ ግን ሁሉም ህይወት በራሱ ልዩና ዕጹብ ስለሆነ አንዱ በሌላው ይተካል ማለት አይቻልም። አቤልም እንዲሁ በሴት ሊተካ አይችልም። ነገር  ግን ሴት አቤል የተመረጠበትን ከድነት ጋር ተያያዥነት ያለውን ዓላማ እንዲያስፈጽም ለሔዋን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ እግዚአብሔር ያስነሳው ዘር ስለሆነ በዚህ ረገድ አቤልን ተክቷል ማለት ይቻላል። ይህንን እውነት ሔዋን በቅጡ ስላስተዋለችም ነው ሴት (እግዚአብሔር ያስነሳው ወይንም እግዚአብሔር የሾመውያለችው።

ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች12 የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ
ዘፍ 424
            ከሄኖስ መወለድ ጋር ተያይዞ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀምረዋል። የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ለእግዚአብሔር መሰዋትን፣ ስሙን እየጠሩ መጸለይን እንዲሁም ስሙን ማወጅን ያካተተ የአምልኮ ተግባር ነው። ለመሆኑ የሄኖስ መወለድ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ከመጀመራቸው ጋ ምን ያገናኘዋልሄኖስ (በዕብራይስጥ ኤኖሽየስሙ ትርጓሜ ሰው ማለት ነው።13 ሔዋን ቃየንን ስትወልድ «ሰው» አገኘሁ ነበር ያለችው። ልብ በሉ ቀደም ብሎ በዚሁ ምዕራፍ ቁ 17 ላይ ቃየን (በያህዌ እርዳታ የተገኘው ሰውሄኖክ የሚባል ልጅ መውለዱን  ብናነብም የሄኖክ መወለድ ለእግዚአብሔር ስም መጠራት ያደረገው ምንም አስተዋጽዖ አልነበረም። እንዲያውም ቃየን  የሰራውን ከተማ በልጁ ስም ሄኖክ ብሎ ጠራው ስለሚል ቃየንና ዘሮቹ ህልማቸው ስማቸውን ማስጠራት እንጂ የእግዘአብሄርን ስም ማስጠራት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።14 ከሄኖክ በኋላ የመጡት ዘሮቹም በእጅ ሙያና በኪነ ጥበብ የሰለጠኑ ይሁኑ እንጂ እግዚአብሔርን በማምለክ የታወቁ አልነበሩም።
            እግዚአብሔር ሴትን ካስነሳው/ከሾመውና እርሱም ሄኖስን (ሰውንከተካ በኋላ የእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ። ለምን እስካሁን ይህ አልሆነምእግዚአብሔር መመለክ እንዳለበት የሚያሳስባቸው አልነበረም ማለት ነውበርግጥ አቤል በህይወት የለም። ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ኮብልሏል። አዳምና ሔዋን በህይወት ቢኖሩም ትኩረቱ ዘሮቻቸው ላይ እንጂ እነርሱ ላይ ባለመሆኑ ስለነርሱ የአምልኮ ህይወት የተባለ ነገር የለም። እግዚአብሔር የመረጠው ዘር ሲነሳ የእግዚአብሔር ስም እንደገና በሰዎች መካከል ተገቢውን ስፍራ አገኘ። እንግዲህ ሄኖስ የጥፋትን ውሃ አምልጦ የእግዚአብሔርን በረከት የሚቀበለውን ትውልድ የሚመራ አዲሱ አዳም/ሰው ነው ማለት ይቻላል።15
            የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን ከተመለከትን እግዚአብሔርን መጥራት የጀመረው ራሱ ሄኖስ ሆኖ እናገኘዋለን።16  የቃየን ዘሮች በራሳቸው ጉዳይ ሲዋከቡ እግዚአብሔርን እያመለከ ሌሎች ሰዎችም እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ማወጅ የጀመረው ሄኖስ ነው ማለት ነው። የጥንቷ ቤተክርስቲያን አበው ሄኖስንና እምነቱን አክብረው ጽፈዋል።17 እንዲያውም ቅኦገስቲን ሴትን እንደ ትንሳዔ ማለትም እንደ ክርስቶስ ሄኖስን ደግሞ እንደትንሳዔው ልጆች ማለትም እንደ ክርስቲያኖች አድርጎ ነበር የሚያያቸው።18
            ወደማጠቃለያው ስመጣ ሔዋን ቃየንን ተስፋ አድርጋ የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር የርሷን ምርጫ ቃየንን ትቶ ታናሹን አቤልን መረጠ። ቃየን በዚህ ጉዳይ ቅንዓት ይዞት እግዚአብሔር የመረጠውን ወንድሙን ገደለ። እግዚአብሔር የመረጠውን ዘር ሴትን እንደገና አስነሳ/ሾመ። ሴትም ሄኖስን (አዲሱን ሰውተካ። ይህም አዲስ ሰው/ዘር ያህዌን አመለከ ሌሎችም እንዲያመልኩት ማወጅ ጀመረ። ከዚያም የተመረጠው ዘር ያህዌን እያመለከ እስከ  ኖኅ ዘለቀ። የሔዋን የእምነት ጉዞም በስተመጨረሻ በእግዚአብሔር የማዳን መንገድ ውስጥ በመገኘት ተጠናቀቀ። በጉዞዋ ሞትን ብታይም ካለማስተዋሏ የተነሳ ማድረግ እያለባት ስላላደረገችው ጉዳይ ንስሃ ገብታለች ብዬ አምናለሁ። በስተመጨረሻም ሞት በትንሳዔ ድል ሆኖ ወደ ኤደን ገነት የመመለስ ተስፋዋ እንደገና አበበ። ታዲያ በዚህ ታሪክ አዲስ  ኪዳንን በጥላነት ብንመለከት ይደንቃልንዘፍ ገና ከጠዋቱ በዚህ ዓይነት መልክ የድነትን ሂደት ማመላከቱ ያህዌ የታሪክ ባለቤትና ጌታ መሆኑን፤ ታሪክንም በዓላማው የሚመራ አምላክ መሆኑን ያሳየኛል።

      ሐዋ ሥራ 2፥ 22-24 እና 36
የእስራኤል ሰዎች ሆይ ይህን ቃል ስሙ ራሳችሁ እንደምታውቁ የናዝሬቱ ኢየሱስ . . . ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም . . . በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሳው ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።

እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።

315 የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን።

48-12 እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረምር፥ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ህዝብም ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።


1 በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የማመሳክራቸው የዕብራይስጥና የግሪክ ብሉይ ኪዳን መጻህፍት የማሶሬቲክ መ/ቅ እና የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በመባል የሚታወቁትን ነው። እነዚህን ጥንታዊ ቅጂዎች የመረጥሁት በየለቱ የምናነባቸውና የምናመሳክራቸው የአማርኛ ቅዱሳት መጻህፍት ችግር ኖሮባቸው ሳይሆን እነርሱን ብቻ መሠረት በማድረግ ማስተላለፍ የፈለግሁትን መልዕክት ማስተላለፍ ስለተቸገርሁ ነው።

2 ወንድ ልጅ ተብሎ የተተረጎመው በዕብራይስጥ «ኢሽ» ፤ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ደግሞ «አንትሮፖስ» ተብሏል። እነዚህ ሁለቱም መጠሪያዎች ለህጻን የሚሰጡ ሳይሆኑ በጠቅላላው የሰው ዘርን ለመወከል አለያም ሙሉ ሰው የሚባል ልክ ላይ የደረሰ ሰውን ለመግለጽ የሚገቡ ናቸው። «ኢሽ» በየትኛውም የብ/ኪ ክፍል ህጻን ልጅን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም (Kenneth A. Mathews. The New American Commentary, Genesis 1-11:26, 1996, 265)

3 የዕብራይስጡን መ/ቅ ከተመለከትን «በእግዚአብሔር (ያህዌርዳታ» የሚለው የሔዋን አባባል በሶስት መንገድ ሊተረጎም ይችላል። (1) በእግዚአብሔር ርዳታ ሰው አገኘሁ፣ (2) እኔም ከእግዚአብሔር እኩል ሰው አፈራሁ፣ (3) እግዚአብሔር የሆነውን ሰው አፈራሁ። እንዲህ ዓይነቱን ያተረጓጎም ልዩነት የፈጠረው በእብራይስጥ «ኤት» የሚባለው መስተዋድድ (ፕሪፖዚሽንነው። ኤት አንዳንድ ጊዜ «ጋር» የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ርቱዕ ተሳቢን (ዳይሬክት ኦብጀክትለማመልከት የሚያገለግለውን በአማርኛ «» የተሰኘው አመልካች ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ዘፍ 11 «እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ» በሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ እግዚአብሔር የፈጠረው ምን እንደሆነ የሚገልጽልን ሰማይ እና ምድር በሚሉት ስሞች ላይ  የተቀጠለው «» ነው። «» ባይኖር እግዚአብሔር መፍጠሩን ብቻ እንጂ ምን እንደፈጠረ ልናውቅ አንችልም ነበር። ሔዋንም «ሰው አፈራሁ «ኤት» እግዚአብሔር (ያህዌ)» ማለትዋ «ከእግዚአብሔር ጋር» ማለትዋ ነው ወይንስ «እግዚአብሔርን» የሚለው አነጋጋሪ ነው። «ከእግዚአብሔር ጋር» የሚለው ንባብ ሔዋን ቃየንን ከእግዚአብሔር የወለደችው ስለሚያስመስል ያንን ለማስቀረት ይመስላል የሰብዓ ሊቃናት ቅጂ «ኤት» የሚለውን «» በሚለው በመተካት «በእግዚአብሔር» የሚል ትርጉም እንዲይዝ አድርጎታል (Mathews, 265 የግርጌ ማስታወሻ)። የ1952 ዕትም የአማርኛ መጽሃፍ ቅዱስ «» የሚለውን ቅጥያ በመጠቀም «ከእግዚአብሔር» ተብሎ እንዲነበብ ያደርገዋል። እንግዲህ የዕብራይስጡ «ኤት» የተሰኘው መስተዋድድ «ጋር፣ ን፣ በ፣ እና ከ» ተብሎ ተተረጉሟል ማለት ነው። እንዲያውም አዲሱ መደበኛ ትርጉም መ/ጽ «ርዳታ» የሚለውን ቃል አክሎ «በእግዚአብሔር ርዳታ» ተብሎ እንዲነበብ አድርጓል።
የአማርኛ ቅዱሳት መጻህፍት ከእግዚአብሔር ወይንም በእግዚአብሔር ርዳታ የሚለውን አነባበብ በመምረጥ ሔዋን የበኩር ልጅዋን  ቃየን በማለት የሰየመችው ህይወትን ሰጪ እግዚአብሔር መሆኑን ለመመስከር ፈልጋ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራሉ። ሁለተኛውን ንባብ በመምረጥ ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር ራስዋን እያፎካከረች እንደሆነ የሚያስቡም አሉ (Cassuto as quoted by Victor P. Hamilton. “The Book of Genesis Chapters 1-17” NICOT, 1990, 221)። ማርቲን ሉተር ሶስተኛውን ንባብ ይመርጣል። ሔዋን ቃየንን እግዚአብሔርም ሰውም የሆነው መሲሑ እንደሆነ አምና ከነበር ስለእግዚአብሔር የደህንነት ዕቅድ ጠለቅ ያለ መረዳት አግኝታለች ማለት ነው። ለዚያም የእግዚአብሔር ዕቅድ ራስዋን የሰጠች እንደሆነ እየመሰከረችም ነው። የሔዋን ስህተት የሚሆነው ያ ዘር የሚመጣበትን ጊዜ አለማወቅዋ ነበር። ምክንያቱም ለሰው ዘር ሁሉ ደህንነትን ያመጣው እግዚአብሔርም ሰውም የሆነው ክርስቶስ የተወለደው በኋለኛዋ ሔዋን በማርያም ነውና።

4 The Brown-Driver-Briggs Hebrew and English Lexicon. Eleventh printing, 2007.  በተጨማሪም ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ጸሁፍ ያመሳክሩ፣ Allan J. Hauser. Linguistic And Thematic Links Between Genesis 4:1-16 and Genesis 2-3. Journal of Evangelical Theological Society. V. 24. no. 4. pp 297-305.

5 በግርጌ ማስታወሻ 4 የተመለከተውን መዝገበ  ቃላት ያመሳክሩ።

6  በመጽሃፈ መክብብ ላይ የምናገኘው ሰባኪ ከጸሃይ በታች ያለ ህይወት ከእግዚአብሔር ውጪ ለመኖር ሲሞከር ከንቱ እንደሆነ ለማሳየት በ12 ምዕራፎች ውስጥ «ሄቬልከንቱ» የሚለውን ቃል ለ37 ጊዜ ያህል ጠቅሶታል።

7 ርብቃ ዔሳው ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብን እንዳይገድለው በጥበብ እሽሽታዋለች (ዘፍ 27፥ 41-46)። ዮሴፍም ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል ባሰበ ጊዜ በህልም ተረድቶ ህጻኑንና እናቱን ማርያምን ወደ ግብጽ አሸሽቷል (ማቴ 213-15)። ሁለቱም የሔዋንን ስህተት አልደገሙም።

8 የኤን አይ ቪ ትርጉም «ሰጠኝ» የሚለውን አነባበብ ይመርጣል። አዲሱ መደበኛ ትርጉምም ከዚያ የተቀዳ በመሆኑ ያንኑ ንባብ ያንጸባርቃል።

9 «ሺት» ዕቃን ማስቀመጥን፣ ሰውን መሾምን፣ እጅን መጫንን፣ አንዳንድ ጊዜም ባንድ ጉዳይ ላይ ሃሳብን ማኖርን እና

 የመሳሰሉትን ድርጊቶች ለመግለጽ ሊውል ይችላል ( ግርጌ ማስታወሻ 4 የተመለከተውን መዝገበ  ቃላት ያመሳክሩ )

10 ESV, ASB, KJV, and Young's Literal Translation ቅጂዎችን መመልከት ይቻላል።

11 «እግዚአብሔር አስነሳልኝ» የሚለው የአዲስ ኪዳን ጸሃፍት የክርስቶስን ትንሳዔ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል ነው። የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚዎች የሴትን መወለድ ከሞት እንደመነሳት ያህል አድርገው ቆጥረው ከሆነ ይህንን ቃል የመረጡት ታሪኩን መሲሃዊ አድርገን ብንወስደው ከተገቢው በላይ ለጥጠነዋል ማለት አይደለም።

12 በዕብራይስጡ ሰዎች አይልም። ይልቁንም «ከዚያም በእግዚአብሔር (ያህዌስም መጥራት ተጀመረ» ነው የሚለው።

13  ግርጌ ማስታወሻ 4 የተመለከተውን መዝገበ  ቃላት ያመሳክሩ ። አንዳንድ የጥንት ቤ/ክ አበው ሄኖስን ልዩ ሰው፣ እግዚአብሔርን የመሰለ፣ እግዚአብሔርን በመምሰል በጽድቅ ህይወት ለሚመላለሱ አማኞች ምሳሌ የሆነ እንደሆነ ያምኑ ነበር (Steves D. Fraade. “Enosh and His Generation Revisited” in Biblical Figures Outside the Bible, eds. Michael Stone and Theodore Bergren, 1998)

14 ከጥፋት ውሃ በኋላ የተነሱትም ትውልዶች ለስማቸው መጠሪያ ከተማ መስራት ጀምረው ነበር (ዘፍ 114)

15 Mathews 290

16 የግሪኩን ዐረፍተ ነገር አገባብ የተመለከትን እንደሆነ «እርሱም በእግዚአብሔር ስም እንዲጠራ ተስፋ አደረገ» የሚል ትርጉም ይሰጣል።

17 ኦሬገን፣ የቂሳሪያው ዩሴቢየስ፣ የሚላኑ አምብሮስ፣ ዓይነ ስውሩ ዲዲሞስ እና ጆን ክሪሶስቶም ይገኙበታል Fraade 68-71

18 የኦገስቲንን መጽሃፍ ቅዱስ አፈታት ያለምንም ጥያቄ እንቀበለዋለን ማለት አይደለም። እርሱ በረበረበት ታሪካዊ ወቅት የነበሩ አይሁድና ክርስቲያን ጸሃፍት የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪካዊ ጽሁፎች በግልጽ የማይታዩ የተደበቁ ውስጠ ወይራዊ (አሌጎሪትርጓሜ አላቸው ብለው ያምኑ ስለነበር ስነ አፈታታቸው ያንን ሲያንጸባርቅ ቢታይ የሚደንቅ አይሆንም። Annette Yoshiko Reed “Reading Augustine and/as Midrash” in Midrash and Context, eds. L Teugels and R. Ulmer (Piscataway, N.J.: Gorgias Press, 2007) 75-131