Thursday, May 31, 2012

Kingdom dynamics



ውድቀት  በቅርበት  ሲጤን

ክፍል  1
አብርሃም  ጌታቸው

ጅማሮ

          ጊዜውን በርግጠኝነት ማስታወስ ቢያቅተኝም ቅድም አያቴ ከሞቱ በኋላ እንደሆነ ግን አልዘነጋውም። «አይዬ» እያልን እንጠራቸው የነበሩት እኚህ ቀይ ቀጭን ሽበታም ሴት ቅድመ አያቴ ከሞቱ በኋላ ሞት ሲመጣ የምሩን እንደሆነ ገባኝ። ሌላ ጊዜ የሌሎችን በር ሲያንኳኳ እንጂ በእኛ አጥር ሲያልፍ አይቼውም አላውቅ። ለነገሩ እኛ ሰፈር ደጋግሞ ያንኳኳ ነበር። አንድ ቀልደኛ አጎቴ የዕድሩን ድንኳን በተደጋጋሚ እየተከሉ ከመንቀል ጎማ ገብቶለት ካንደኛው ቤት ወደሌላኛው ተገፍቶ ቢሄድ ይሻላል ብሎ ነበር።
          ታዲያ አንድ ቀን ወላጆቻችን እውጭ ስላመሹ በምድጃ ከሰል አንድደን እሳቱን እየሞቅን እንጠብቃቸው ነበር። ሁልጊዜም እንደምታደርገው ወርቄ የምንላት እህታችን ምድጃውን ወደራሷ አስጠግታ የእሳቱን ሙቀት በሞኖፖል ይዛዋለች። እንቅልፍ እያንጎላጃት ስለሆነ እሳቱ ላይ ድፍት እንዳትል ስቅቅ እያለን ባይናችን እናቃኛታለን።
          የቤታችን አንደኛው ግድግዳ ላይ የአዳምና ሔዋን ስዕል ተሰቅሏል። ኑሮ እንደተመቻቸው የሚያስታውቁ በዛፎች  መሃል እርቃናቸውን የሚመላለሱ ወርቃማ ጸጉርና ሰማያዊ ዓይኖች ያሏቸው ፈረንጅ ወንድና ሴት። ስዕሉን ብዙ ጊዜ ተመልክቼዋለሁ። ከተሰቀለበትም አውርጄ ወረቀቶች ቀጣጥዬ አተልቄ ስዬዋለሁ። የኔ አዳምና ሔዋን በነጭ ወረቀት ላይ በጥቁር እርሳስ የተሳሉ ከመሆናቸው በቀር ከዋናው ስዕል እምብዛም አይለዩም ነበር። ምናልባትም ጠቁረው ሲታዩኝ ቅማንቶቼ እንደሆኑ እንዲሰማኝ ብዬ እንደሆን የሳልኋቸው ለኔ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ቢሆንም ግን ስለነርሱ በጥልቀት እንዳስብ ምክንያት ሆነልኝ።
          ወርቄ በድንገት «ምናለ ሞት ባይኖር» አለች። ጉዳዩን ያነሳችው ሳናስበው ስለነበር ምን መመለስ እንዳለብን ጠፋን። ለነገሩ ምንስ ልንላት እንችል ነበርየአይዬ ካጠገባችን መለየት ስለሞት አጥብቃ እንድታስብ እያደረጋት  ነው። «አዳምና ሔዋን የበለሷን ፍሬ ባይበሉ እኮ ሞት አይኖርም ነበር» አለች ቀጠለችና። ቀና ብዬ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ስዕል እንደገና ቃኘሁ። ለካ ሞትን ያመጡብን እንዲያ አምረው በዛፎች መሃል የሚንሸረሸሩት ነጫጭ ወንድና ሴት ናቸው። «አዳምና ሔዋን» አልኩ በልቤ ቁጭት ቢጤ እየተሰማኝ። ለምን ፍሬዋን በሉምን  ነካቸውበእኛ ላይ ሞት እንደሚያመጡብን እንዴት አልታያቸውምአልኩ። ከሞት ማምለጫው ስላልታየኝ ከዚያ በኋላ የነበረው ምሽት ይበልጥ ድቅድቅ ጨለማ ነበር።
          ለመሆኑ ሞት የፍጥረት ሁሉ ፍጻሜ ነውህይወት ከሞት ባሻገር ቀጣይነት አለውከሆነስ እንዴትበጨቅላ አእምሮዬ ስለነዚህ ጥያቄዎች ማሰብ ለጊዜው አስፈሪ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቆሜ ገጠመኙን ስቃኘው ግን በእግዚአብሔር የድነት ዕቅድ ውስጥ ለመገኘት መንገድ እንደጀመርሁ ጠቋሚዎች ነበሩ። ሞት በምድር ላይ የሚኖር ህይወት ያለው ፍጡር ሁሉ የሚያጋጥመው ነገር ቢሆንም ማናችንም በየለቱ ስለርሱ እያሰብን አንኖርም።  እኔም በዚህ ጽሁፍ ስለሞት የተነገሩ ጉዳዮችን እያነሳሁ ለመዳሰስ አልሞክርም። የጽሁፌ ዓላማ ከላይ ባነሳሁት ገጠመኜ ውስጥ ወርቄ ስለሞት ያላት ምልከታ ምን ያህል ተአማኒነት እንዳለው ለመመርመር ነው። ለመሆኑ ወርቄ  ልክ ነበረችሞት በሰው ልጆች ላይ የነገሰው አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ፍሬ ስለበሉ ነውንወይንስ ንጽረተ ዓለሟን የቀረጹት ባህልና ሃይማኖት የሰጧት ትንታኔ ስለሆነለመሆኑ እነዚህ ትንታኔዎች ምን ያህል እውነትነት አላቸውመጽሐፍ ቅዱስስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል?1
          ለነዚህ ጥያቄዎች መንደርደሪያ የሚሆኑ ጭብጦችን ለማግኘት የዘፍጥረትን መጽሃፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች መነሻ  ማድረግ ይኖርብኛል። በተለይም ምዕራፍ እና 3። ዘፍጥረት የጅማሬዎች መጽሃፍ ስለሆነ ስለ ፍጥረት፣ ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ድነት ጅማሬ ይነግረናል። በተጨማሪ ስለ ሞት የተነሱ ጉዳዮችም አሉ። ስለነዚህ ጉዳዮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆኑ አንዳንዴም ተቃራኒ ይዘት ያላቸው ትንታኔዎች የሉም ማለት አይደለም። የእኔ አተያይ ግን የእግዚአብሔር ርዕዮት ከሆነው ከመጽሃፍ ቅዱስ አንጻር ነው። እግዚአብሔር ስለ ፍጥረት ያለውን ክቡር ዕቅድ የሚነግረን መጽሃፍ ቅዱስ ነው። ታዲያ ይህንን ማለት መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በዚህ ዘመን የምንኖር ሰዎች የምናነሳቸውን ሳይንሳዊና ታሪካዊ ጥያቄዎችን ሁሉ የኛን ፍላጎት በሚያረካ መልክ ይመልስልናል ማለት አይደለም።2 ለነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን እንድናውቅና በርሱ የድነት ዕቅድ ውስጥ እንድንጠቀለል ለማድረግ እንጂ ለሳይንሳዊ ምርምር እንዳልተጻፈ መርሳት የለብንም። ይህ እንዲህ ከሆነ ሞት እንዴት ተከሰተማምለጫ አለው ወይከሆነስ እንዴትየሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ከእግዚአብሔር አንጻር መልስ የሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ እናገኘዋለን።

በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ

እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ «በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ  ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።»
ዘፍ 216-17

1እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ትዕዛዝ ፦

          እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው በኤድን ገነት ውስጥ አስቀመጠው (ዘፍ 28)። በመቀጠልም ለሰው ምግብ ሊሆኑ የሚችሉና ለዓይን የሚያስደስቱ ዛፎችን ፤ እንዲሁም የሕይወት ዛፍንና መልካምንና ክፉን መለየት የሚያስችለውን የዕውቀት ዛፍ አበቀለ (29)። አዳምንም የህይወትን ዛፍ ጨምሮ ከፈለገው ዛፍ ፍሬ እንዲበላ ፈቅዶለት መልካምና ክፉ የሚያሳውቅ የተባለውን ዛፍ ብቻ እንዳይበላ አዘዘው። አንድ መቶ የዛፍ ዓይነቶች ቢኖሩ ከነዚያ ውስጥ አንዲቱን ብቻ ከልክሎ ዘጠና ዘጠኙን እንዲበላ እንደመፍቀድ ማለት ነው። እንግዲህ ምን ሊባል ይችላልእግዚአብሔር እንደሆን የምድር ባለቤት ነው። እንደባለቤት የወደደውን መስፈርት ማስቀመጥ ይችላል። ሰው እግዚአብሔር ለክብሩ በሰራው ዓለም ውስጥ በርሱ መስፈርት ሊኖር የተጠራ/የተጋበዘ ባለ አደራ  እንጂ ባለቤት አይደለም። ለዚህም ነው እግዚአብሔር ባዘጋጀው ምድር ላይ ለመኖር መስፈርቶቹን ማሟላት ተገቢ የሚሆነው።3
          እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው ትዕዛዝ ባንድ በኩል ፈቃድን የሚሰጥ በሌላ በኩል ደግሞ ክልከላ ያለበት ሆኖ ሳለ ብዙ ጊዜ ትኩረት ሲሰጠው የምናየው ክልከላው መሆኑ ግርም የሚል ጉዳይ ነው። ሰው የህይወትን ዛፍ ጨምሮ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ያሉትን ዛፎች ሁሉ እንዲበላ ታዟል።4 ገደብ የተደረገበት ከዕውቀት ዛፍ እንዳይበላ ብቻ  ነበር። እግዚአብሔር ለሰራቸው ነገሮች ገደብ ሲያበጅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዘፍ 19-10 መሠረት ባህር የብስ የሚባል ዳርቻ/ገደብ አለው። ይህንን ገደብ አልፎ የሄደ ለት ጥፋት ያስከትላል። ጸሃይ የምትሰለጥነው በቀን ጨረቃ ደግሞ በለሊት ነው (ዘፍ 116)። ጸሐይ ገደብዋን አልፋ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ እኔ ብቻ ልሰልጥን ብትል ከቃጠሎዋ የተነሣ ህይወት ከምድረገጽ ይጠፋ ነበር። ጨረቃም በበኩልዋ እንዲሁ ብትል ሁሉ ነገር በቅዝቃዜ ወደ በረዶነት ተቀይሮ በምድር ላይ ህይወት ያከትም ነበር። የባህር እንሰሶችም ቢሆኑ  በውሃዎች ውስጥ ይኖራሉ እንጂ በምድር ላይ ለመኖር አይሞክሩም። ዕጽዋትም በምድር ላይ ይበቅላሉ እንጂ እንደ ሰማይ ወፎች ለመሆን አያምራቸውም። ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔር በዘረጋለት መንገድ ላይ ሲጓዝ እግዚአብሔር ስራውን ከፈጸመ በኋላ ያየው መልካምነት ዘላቂ ይሆናል።
          እግዚአብሔር በሰው ላይ ገደብ ያስቀመጠው እርሱ በሰራው ዓለም ውስጥ ያለውን ላቅ ያለ የተትረፈረፈ ህይወት  እንድናጣጥም እንጂ ነጻነታችንን ለመጋፋትና ደስታችንን ለማደብዘዝ አይደለም። ታዲያ ይህ ምን ችግር አለበት?  ለመሆኑ በዓለም ላይ ለምናደርጋቸው ነገሮች መመሪያዎች ባይኖሩ ህይወት ቅጥ አያጣም ወይእስቲ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ መኪና የሚያሽከረክሩ አንዳንዶች የቀኝ መስመራቸውን ትተው እንደለንደን አሽከርካሪዎች በግራ መስመር ላይ ማሽከርከር ቢጀምሩ ምን እንደሚፈጠር ላፍታ አስቡትየትኛውም የህይወት መስክ ያለ መመሪያ ፈር ሊኖረው አይችልም። ታዲያ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ «ለምን ይህ ትዕዛዝ ተሰጠእግዚአብሔር አዳም  እንደሚወድቅ እያወቀ ለምን ያቺን ዛፍ አበቀለ?» እና የመሳሰሉትን ፋይዳቸው እምብዛም የሆኑ ጥያቄዎች ሲያነሱ ይታያሉ። ለነገሩ ጥያቄዎቹ በወጉ ከተጤኑ ለሰው ውድቀት ተጠያቂው እግዚአብሔር ነው እንደማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥሩ ጠያቂ መሆን ምንኛ መታደል ነውመልስ ሊገኝላቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ማብቂያ ወደሌለውና ወደማያንጽ መላምት ውስጥ ከመግባት ያድናል። ስለዚህ «እግዚአብሔር እያወቀ ለምን ለሰው ውድቀት ምክንያት የሆነ ዛፍ አበቀለ?» ከማለት ይልቅ «አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን የዛፍ ፍሬ ለምን በሉ?» ብሎ መጠየቁ ይሻላል።

2መልካምንና ክፉን ማወቅ ፦

          መጽሐፍ ቅዱስ የዕውቀትን ዛፍ የጠራው «መልካምንና ክፉን የሚያሳውቅ» በማለት ስለሆነ እንደዚያው ልንወስደው ይገባል። የህይወት ዛፍ የተባለው ህይወትን እንደሚሰጥ ልክ እንዲሁ የዕውቀት ዛፍ የተባለው ዕውቀትን የሚሰጥ ዛፍ ነው።5 ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ወይንም ዛፉ አንዳች ዓይነት ዕጽ ይኑረው አላውቅም። ለነገሩ እባብም አውርቷል። እንዴት እንዳወራ የሚያውቅ ካለ ቢነግረኝ እወዳለሁ። ስለዚህ ዛፉ ፍሬው ተቀጥፎ ሲበላ መልካምንና ክፉን መለየት የሚያስችል ዕውቀት ይሰጣል ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ዕውቀት  መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮችን መለየት የሚያስችል የጥበብ ልክ ላይ መድረስን የሚያሳይ ነው።6 ጎርደን ዌንሃም የተባለው ጸሃፊም «መልካምንና ክፉን ማወቅ» የተባለው ለእግዚአብሔር ብቻ የተወሰነውን «ጥበብ» አመልካች ነው ይለናል።7
          በየትኛውም ዘመን የሚነሳ ትውልድ ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር ያለውን የህይወትን ቁም ነገር መጨበጥ መቻል ናፍቆቱ ይመስለኛል። የህይወት ዓላማ፣ ትርጉም እና ፍጻሜ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሚደረገውም ምርምር ክቡር ተግባር ነው። ለዚህ ታዲያ የእግዚአብሔር እርዳታ ያስፈልጋል። ከእግዚአብሔር በሚገኝ መገለጥ  ላይ ሳንደገፍ ለህይወት ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መሞከር እግዚአብሔርን የጣለ ሌጣ ሰብዓዊነት ነው።  በእግዚአብሔር ላይ በቋሚነት መደገፍና ፈቃዱን መጠየቅ ሳይኖር፤ ሰው የእግዚአብሔርን ቦታ ተክቶ እግዚአብሔር በሰራው ዓለም ላይ ያለ እግዚአብሔር ድምጽ ራሱ የራሱ እግዚአብሔር ሆኖ ለመኖር መወሰን ፍጻሜው አያምርም። በዚህ ዓይነት መንገድ የሚገኘው ዕውቀት በማናቸውም የህይወት ጉዳይ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጭ ሰውን የሚያደርግ ስለሆነ ለእግዚአብሔር ቦታ የለውም። እግዚአብሔርም ሰው ከዚህ ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ የከለከለው ለዚህ ነው እንጂ እውቀት ጠሊታ ሆኖ አይደለም። እንዲያማ ካልሆነ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት ደናቁርት ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ልንደርስ ነው ማለት ነው። በመሠረቱ እግዚአብሔር ሰውን ምድርንና ሞላዋን እንዲገዛና እንዲመራ ተናግሮት ያንን ተግባር በድንቁርና ያከናውነዋል ብሎ ሊያሰብ አይችልም። ጉዳዩ የእግዚአብሔርን ዓለም ለመምራት የእግዚአብሔር እርዳታ ያስፈልጋል ለማለት  ታስቦ እንጂ። እግዚአብሔር ብቻ ነው እግዚአብሔር የማያስፈልገው። እርሱ በራሱ ሙሉ ስለሆነ ለሚያከናውናቸው ተግባሮችም ሆነ ለሚወስናቸው ውሳኔዎች መገለጥ ወይንም ምክር የሚሰጠው ማንም የለም። ሰው ግን እግዚአብሔር ስላልሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔር ያስፈልገዋል።
እነዚህ ትዕዛዛት የሚያመለክቱት ለሰው ልጅ መልካም የሆነውንና ያልሆነውን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር በሰራቸው መልካም ነገሮች እንድንደሰት እርሱን ልንታመነውና ልንታዘዘው ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በእግዚአብሔር ላይ ካመጽን ግን  በራሳችን መልካም የሆነውንና ያልሆነውን መለየት ይኖርብናል። እንዲህ አይነቱ ህይወት በዘመናችን ላለው ሰው ተመራጭ ቢመስልም የዘፍጥረት ጸሃፊ ግን በሰው ዘር ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ መጥፎ ነገሮች ሁሉ የከፋ ዕጣ ነው ይለናል።8

3ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ ፦

          አዳምና ሔዋን ከዕውቀት ዛፍ ፍሬ የበሉ ቀን አልሞቱም። እንዲያውም አዳም 930 ዓመት ከኖረ በኋላ ነው የሞተው (ዘፍ 55)። ታዲያ ሞት የተባለው ምን አይነት ሞት ነውሞት ሶስት ዓይነት ነው፦ መንፈሳዊ ሞት፣ ስጋዊ ሞትና ዘላለማዊ ሞት እያልን ክፍሉ የሚፈጥረውን ግራ መጋባት ለመፍታት መሞከራችን ክፋት የለውም። ችግሩ እንዲህ ዓይነቱ ትንታኔ ክፍሉን በጥልቀት ለመረዳት ከመሞከር ሊያግደን መቻሉ ነው። ምክንያቱም መልሳችንን  አግኝተናልና።
          እስቲ ለአፍታ ከዚህ አለፍ ብለን እናስብ። በመጀመሪያ ደረጃ አብዛኞቹ የመጽሃፍ ቅዱስ አጥኚዎች በዘፍጥረት መጽሃፍ ውስጥ መንፈሳዊ ሞት የሚል ሃሳብ ባለመኖሩ እግዚአብሔር ስለመንፈሳዊ ሞት ነው የተናገረው ለማለት  አይደፍሩም። ይህ የአዳምና ሔዋን ታሪክ በእስራኤላውያን መካከል ሲተረክ ሞት እነርሱ የሚያውቁት ሞት እንጂ  አዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳን ተብሎ የተጠናቀቀ ቀኖና ያለን ሰዎች የምናውቀውን አይደለም። ለእኛ ሞት ሶስት ዓይነት ሊሆን ይችላል። ለነርሱ ግን ሞት ያው አንድ ሞት ነው። ማለትም እግዚአብሔር በሰጣቸው በሰፊይቱና በመልካሚቱ ምድር ላይ ያለውን በረከት እንዳይበሉ ከህይወት መወገድ። አንዳንድ ጊዜ በህይወት እያሉም እግዚአብሔር በክብሩ ከሚገኝበት ህዝብና ምድር በሚለዩበት ጊዜ እንደሞቱ ያህል ይቆጠራል።9 የእስራኤል ወደ  ባቢሎን መማረክ እንደሞት ያህል ነበር። ለዚህም ይመስላል በሕዝቅኤል 37 በምርኮ ያሉት የእስራኤል ህዝብ እንደሞቱ ያህል ተቆጥረው ከምርኮ መመለሳቸው ከሞት እንደመነሳትና ከመቃብር እንደመውጣት ሆኖ የተነገረው። ስለዚህ ሞትን ትሞታለህ የሚለውን የእግዚአብሔርን የፍርድ ቃል እንዲህ መረዳት ይሻላል።

ፈተና

እባብ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኮለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ «በእርግጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ 'በአትክልቱ  ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉብሎአልን?» አላት።
ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ «በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) 'በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁብሎአል።»
እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ «መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምንና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር  (ኤሎሂምእንደምትሆኑ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ስለሚያውቅ ነው።»
                                                                                                ዘፍ 31-5

4ተናጋሪ እባብ?

          ለማንኛውም አንባቢ የመጀመሪያው አስደንጋጭ ነገር የሚሆነው እባብ ማውራቱ ነው። እንዴት ብሎ አወራድሮ ድሮ እባብ ያወራ ነበር ማለት ነው ወይወይንስ በምልክት ቋንቋ ነው ያዋራትተንኮለኝነቱ የመናገር ችሎታን ለማታለል መጠቀሙ ይሆንእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ያላቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም እባብ እንዴት እንዳወራ አልተጻፈልንም። እንዲያ ከሆነ ደግሞ የዘፍጥረት ጸሃፊም ሆነ የመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች እባብ ማውራቱን መቀበል አልቸገራቸውም ነበር ማለት ነው። ስለዚህም ጸሃፊው ምንም ዓይነት ፍንጭ ሳይሰጠን  አልፏል። ይህ ጉዳይ ጥያቄ የሚሆንብን በዚህ ዘመን ያለነው ሰዎች እንጂ የዘፍጥረት ጸሃፊም ሆነ ተደራሲዎች አይደሉም። ስለሆነም የኛን ፍላጎት በሚያረካ ልክ መልስ አልሰጠንም።10
          በሌላ በኩል ግን ሌሎች የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎችን ስናይ ከእባቡ በስተጀርባ ሌላ አካል እንደነበር ይነግሩናል። የእዮብን ፈተና ከተመለከትን ለእዮብ ለጊዜው ባይታወቀውም የኢዮብን ታሪክ ለምናነብ ለኛ ግልጽ የሆነልን የኢዮብ ፈተና የጀመረው ከሰይጣን መሆኑ ነው (ኢዮ 1-2)። የኢዮብ አገልጋዮች በየተራ እየመጡ ሰዎችና የተፈጥሮ ኃይላት ስላደረሱበት ጥፋት ሲነግሩት ከእነዚህ ነገሮች በስተጀርባ ስለነበረው ሰይጣን የሚያውቁት ነገር  ባለመኖሩ ያንን አስመልክቶ ያሉት ነገር አልነበረም። ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ በአጋንንትና በሰይጣን ኃይል ላይ ስላላቸው ስልጣን ሲነግራቸው «ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ» ነበር ያላቸው (ሉቃስ 1017-20)። ሐዋርያው ዮሃንስ በራዕይ 129 «ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያቢሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው» በማለት ይህ እባብ ሰይጣን እንደነበር ይመሰክራል።
          ወደ ዘፍ ስንመለስ ሔዋን ከእባቡ በስተጀርባ እግዚአብሔር ለፍጥረት ያለውን መልካም ዕቅድ የሚቃወም አካል መኖሩ የተገለጠላት አይመስልም። እግዚአብሔር ከፈጠራቸው የምድር አራዊት መካከል ካንዱ ጋር እያወራች ነበር የመሰላት። እባቡ ግን ያደረገው አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲተላለፉ ያደረጋቸውን  አውድ (c o n t e x t) መፍጠር ነበር። አዳምና ሔዋን የወደዱትን ለማድረግ ነጻነት ያላቸው ሰዎች ቢሆኑም የሚያደርጉት ውሳኔ ከተረዱትና ከመሰላቸው ነገር በመነሳት ነው። ከዚህ አንጻር ከታየ አዳምና ሔዋንም ሆኑ የሰው ዘር በሙሉ የወደድነውን ለማድረግ ያለን ነጻነት ፍጹም ነው ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም የመጣነው በምርጫዎቻችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁኔታዎችና ስርዓቶች ወዳሉበት ዓለም ነውና። ታዲያ ይህ ማለት  እግዚአብሔር የሰራቸው ነገሮች እባብ፣ የሚያምር ዛፍ፣ ፍቅርና ወዳጅነት ለሰው ውድቀት ምክንያቶች ናቸው ማለት አይደለም። ስለሆነም ከእባቡ ጀርባ ሰይጣን እንደነበር ማሰቡ ክፍሉን ለመረዳት አስተዋጽዖ ማድረጉ ብቻ  ሳይሆን ነገሩ እውነትነት ስላለውም ነው። አዳምና ሔዋንም የመጡት ያለምንም ተጽዕኖ በራሱ ነጻ ምርጫ ዓመጽን  የመረጠና በእባቡ አማካይነት በገነት መካከል መገኘት የቻለ ሰይጣን/ዲያቢሎስ ወዳለበት ዓለም ነው።11 ስለዚህ  ለምርጫዎቻቸውና ለውሳኔዎቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ማዕከል ማድረግ አማራጭ የሌለው ነገር ነው ማለት ነው።
          የዘፍጥረት ጸሃፊ እባቡ የሚናገራቸውን ነገሮች በጥንቃቄ እንድናያቸው ስለፈለገ ስለእባቡ ተንኮለኝነት አስቀድሞ  ነግሮናል። እባብ ለሴቲቱ ጥያቄ ሲያቀርብላት ቅንነት ያለበት ይምሰል እንጂ ተንኮል የተሞላበት እንደነበር ካጠያየቁ ያስታውቃል። እስቲ ጥያቄውን እንመልከት ፦
«በእርግጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ 'በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉብሎአልን?» አላት።
የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ደግሞ እንመልከት ፦
«በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን  መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ»
          የእባቡ አጠያየቅ «እግዚአብሔር በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ከማናቸውም ዛፎች እንዳትበሉ ብሏል፤  አይደል እንዴ?» አይነት ነው። ልብ በሉ እባብ ተንኮለኛ ነው ስለተባለ የሚጠይቀው የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅም መታዘዝም ፈልጎ አይደለም። ዓላማው በሴቲቷ ውስጥ ጥርጥር ለመዝራት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።12 እባቡ ጥያቄውን የጀመረው «በርግጥ» በሚለው ቃል ነው። በርግጥ እግዚአብሔር ብሏል ወይሲናገር ሰምተሻል ወይለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ነሽእንዲህ አይነቱ አጠያየቅ ስላየውና ስለሚያውቀው ነገር ሊመሰክር በፍርድ አደባባይ የተሰየመውን ሰው ምስክርነት ዋጋ ለማሳጣት በጠበቆች ተግባር ላይ የሚውለውን የመስቀለኛ ጥያቄ አቀራረብ ይመስላል። የእንዲህ አይነቱ ጥያቄ ዓላማ መስካሪው አየሁ ሰማሁ ብሎ ስለሚናገርለት ጉዳይ የነበረውን እርግጠኝነት ፍርድ ቤቱ እንዲጠጣጠረው ማድረግ ነው።  እባቡም ለማድረግ የሞከረው ይህንን ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ሃሚልተን የተባለው ጸሃፊ እንዲህ ይላል ፦
ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በተናገራቸው ቃላት መግለጽ የፈለገው በነገሩ መገረሙንና መደንገጡን ስለሆነ ንግግሩ እንደ ጥያቄ መታየት የለበትም። የእግዚአብሔርን ክልከላ በሚሰቅቅ መልኩ በማጋነን ከዛፎቹ አንዳቸውንም እንዳይነኩ እንዳገዳቸው ለማስመሰል ሞክሯል። እንዲህ ዓይነቱ ማስመሰል እባቡ ራሱ የፈጠረው ማጭበርበር ከመሆኑ ባሻገር በሴቲቱ አዕምሮ ውስጥ እግዚአብሔርን ተራ፣ ክፉ፣ ከተገቢው በላይ ቀናተኛና ራስ ወዳድ የሆነ አድርጎ ለመሳል መጣሩም ጭምር ነው።13
          እባቡ በዚህ መንገድ ሰውን ሲፈትን ሔዋን የመጀመሪያዋ ትሁን እንጂ ከርሷ በኋላ የሰውን ዘር በሙሉ በተመሳሳይ መልኩ እየፈተነ ይገኛል። እግዚአብሔር በቸርነቱ እንዲበሏቸው የፈቀደላቸው እልፍ አዕላፋት ዛፎች  እያሉ የተከለከሉት አንዱ ላይ ብቻ ላይ እንዲያተኩሩ ፤ እሱንም ባለመብላታቸው ዋጋው ሊተመን የማይችል ጥቅም እንደቀረባቸው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ታዲያ ይህ የእባብ ብቻ ስራ ነው ለማለት ይቻላልሰው እግዚአብሔር በመደበለት ነገር መርካት እያቃተው በሰይጣን ፈተና ውስጥ ሲወድቅ እያየን አይደለምን?

5ቅን ሴት ፦

ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ «በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) 'በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁብሎአል።»

          ስለዚህ ነገር ምን ልንል እንችላለንበመጀመሪያ ደረጃ ሴቲቱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በትክክል የጠቀሰችው አይመስልም። እግዚአብሔር እንደገና ሔዋን ባለችበት እንዳትነኩት የሚል ትዕዛዝ ካልሰጠ በቀር ከየት አምጥታ «አትንኩት» የሚለውን ልትጨምር እንደቻለች ግልጽ አይደለም። ወይንም ደግሞ አዳም ለሚስቱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በትክክል ሳያስተላልፍ ቀርቶ፤ አለያም ሚስቲቱ በራስዋ በትዕዛዙ ላይ ጨምራበት ከሆነ  ያጋነነችው አላውቅም። ምናልባትም ዛፉን መብላት የሚያስከትለው ሞት የፈጠረባት ጭንቀት ሊኖርም ያችላል።14 አንድ እርግጠኛ የሆንኩበት ነገር እግዚአብሔር እንዳትነኩት አለማለቱን ነው።15 ሴቲቱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ቃል በቃል አለመጥቀሷ ያን ያህል መጋነን የለበትም። የአዲስ ኪዳን ጸሐፍትም ቢሆኑ ሁል ጊዜ ብሉይ ኪዳንን ቃል በቃል ይጠቅሱ ነበር ማለት አንችልም። የዘፍጥረትም ጸሃፊ ስለዚህ አድራጎቷ ሔዋንን ሲኮንናት አናየውም። እንዲያውም ሔዋን በቅንነት የእባቡን ስህተት ለማረም እየሞከረች ነበር ብሎ ማሰብ ይሻላል።
          ከዚህ ይልቅ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የሔዋን ስህተት ከባሏ ውጪ እባቡን ለማዋራትና ለማረም መሞከሯ ነው። እባቡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ሆነ ብሎ በማጣመም ሴቷን ወጥመዱ ውስጥ ለመጣል ተዘጋጅቶ  የመጣ አሳች ነው። እርሷ ይህንን ዕቅዱን አላወቀችም። ተገቢው አካሄድ መሆን የነበረበት እባቡን ከባልዋ ከአዳም ጋር ሆና መጋፈጥ ነበር። ማለትም ከባልዋ ጋር ባላት ኅብረት ውስጥ እባቡ ያመጣው ጥያቄና ሃሳብ መመርመር ነበረበት። ሔዋን ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የቱንም ያህል የማያወላዳ መሆኑን ለማሳየት«አትንኩት» የሚለውን ትዕዛዝ በእግዚአብሔር ስም ብትጨምርም ቃሉ በህይወትዋ ስር ሰዶ ነበር ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱም እባቡ የነገራትን አምና እግዚአብሔር የተናገረውን ለመጣስ ብዙ አልተቸገረችምና።
          እንደው ለነገሩ በሔዋን ላይ ይህን ያህል ደፍሬ ተናገርሁ እንጂ ከሌሎች የተላለፈልንን የእግዚአብሔርን እውነት በስማ በለው ከማስተጋባት ባለፈ ምን ያህል በጥልቀት ተረድተነዋል የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን ልንጠይቀው ይገባል ባይ ነኝ። ከእግዚአብሔር እንደሆነ አስረግጠን ስለምንናገርለት እውነት ብቻንንን መልስ መስጠት ቢኖርብን ስንቶቻችን እስከመጨረሻው እንጸናለንለዚህ እኮ ነው ኅብረት የሚያስፈልገን። እግዚአብሔር ህይወታችን እንዲያብብ፣ እንዲመከር፣ እንዲታረምና ከስህተት እንዲመለስ በኅብረት ውስጥ እንድንኖር መድቦልናል። በክርስትና የተናጠል ጀግንነት አያዋጣም። የሆሊዉድ የፊልም ኢንደስትሪ የሚያሰራጫቸው ግለኝነት ላይ ያተኮሩ  ፊልሞች አስተሳሰባችንን እንዲጫኑት አንፍቀድ። እነርሱ የአሜሪካንን ግለኛ አስተሳሰብ የሚያስታጋቡ ምዕራባዊ  የባህል ነጸብራቆች እንጂ የእግዚአብሔር እውነት አይደሉም።
          ሌላኛው የሔዋን ስህተት በመልሷ ሞት ማዕከላዊውን ስፍራ እንዲይዝ ማድረጓ ነበር። ይህ ለእባቡ የተንኮል ስራ በር ከፋች ሆኖለታል።16 ሔዋን ሞት ጭንቀት እንደፈጠረባት ከመልሷ ያስታውቃል። ተንደርድራ ስለሞት ፍርድ  የተነገረው ነጥብ ላይ ለመድረስ እግዚአብሔር ያለውን እንኳ በወጉ አልጠቀሰችውም። የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዛችን እግዚአብሔርን ከማክበር ከመውደድና ከመፍራት በመነጨ ሳይሆን ትዕዛዙን መጣስ ሊያስከትል የሚችለውን ቅጣት እያሰብን ከሆነ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ዓላማ ተገቢውን መረዳት አግኝተናል ማለት አልችልም። ፍርድ ባይኖርስሲዖልም ገሃነምም ለማስተማሪያነት የሚያገለግሉ ምሳሌያዊ አገላለጾች እንጂ እውን  አይደሉም ብንባል እንዳሻን እንኖር ነበርንእንደ ሔዋን ከሆነ አዎን ነው መልሱ። እግዚአብሔርን ለሚያውቅ ሰው የሲዖልና የገሃነም መኖር ወይንም አለመኖር እግዚአብሔርን በመታዘዝ ረገድ ለውጥ ይፈጥራሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም እግዚአብሔርን ስለሚያውቅና ስለ ኅሊና ሲል በቃሉ ይኖራልና።

ይቀጥላል


1አንዳንዶች ለነዚህ ጥያቄዎች ክሽን ያለ መልስ እንዳላቸው አውቃለሁ። ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከዚህና ከዚያ ጠቅሰው መልስ ይዘው ከተፍ ሊሉ እንደሚችሉም እገምታለሁ። ዳሩ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አንዳንድ ጊዜ የተነሱትን ጉዳዮች በጥልቀትና በስፋት ለማየት እንቅፋት ሊሆን መቻሉ ነው።

2Wenham, Gordon J. Word Biblical Commentary Vol.1. Genesis 1-15. Eds. David A Hubbard and Glenn W. Barker. 1987. pp lii-liii

3Brueggemann, Walter. Genesis: Interpretation. A Bible Commentary for Teaching and Preaching. Ed. James Mays. 1982 p. 51

4«ብላ» መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው። በርግጥ አዳም እግዚአብሔር ያዘጋጃቸው ዛፎች የሚያፈሯቸው ፍሬዎች ለዐይን ስለሚያምሩና ለመብልነት መልካም ስለሆኑ እንደወደደ ሊበላቸው ይችላል። በሌላ በኩል ግን ፍሬዎችን የሚበላው ስላማሩት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንደሆነ ካሰበ በመብላቱ ፍላጎቱን ማርካት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ያከብራል ማለት ነው።

5Wenham 62, በዘፍ 322 የህይወት ዛፍ የተባለው ለዘላለም በህይወት ለመኖር የሚያስችል ዛፍ እንደሆነ ተመልክቷል።

6 Mathews, Kenneth A. The New American Commentary Vol. 1A. Genesis 1-11:26. Ed. E. Ray Clendenen. p. 202

7የግርጌ ማስታወሻ ቁ 5 ገጽ 63 ን ይመልከቱ።

8Sailhamer, John H. The Pentateuch as narrative: A Biblical Theological Commentary. Grand Rapids, MI: Zondervan Publishing House. 1992. p. 101  (የጸሃፊው  ትርጉም )

9Wenham 74-75

10ይህ ማለት ግን ሰዎች በየዘመናቱ ለጉዳዩ መልስ ለመስጠት አልሞከሩም ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአፈ ታሪኮች ምትሃታዊ ሃይል እንዳለው የሚነገርለት ገጸ ባህሪ፣ የሰው ልጅ ሁሉን ለማወቅ ያለውን ጉጉት ወካይ ባህሪ፣ እንደ ካሱቶ አባባል ከሆነ እባቡ የሰው ወካይ ባህሪ ሲሆን ሔዋን የሰማችውም በአእምሮዋ ውስጥ ያለውን የራስዋን ድምጽ ነው (Mathews 233)

11Reno, R. R. Brazos Theological Commentary on the Bible: Genesis. 2010. pp 81-83

12Wenham 73

13Hamilton, Victor P. The Book of Genesis Chapter 1-17: NICOT. Ed. Robert L. Hubbard Jr. 1990 pp 188-89  (የጸሃፊው  ትርጉም)

14Fretheim, Terence E. The Book of Genesis in The New Interpreter Bible Vol. 1. Ed. Leander E Keck. P 360.

15በአይሁድ ሚድራሽ ሔዋን የመለሰችውን የመለሰችው ባልዋ አዳም አትንኩትም ብሏል ብሎ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ ጨምሮ ለሚስቱ በመንገሩ ነው። ሴቲቱም ፍሬውን ስትነካ ምንም አደጋ ሳያስከትልባት ስለቀረ ባልዋ እንደዋሻት በመገመት የሰይጣንን ውስወሳ ልታምን ቻለች። ሞትና ህይወት ያሉት በምላስ ላይ ነው። አዳምም እግዚአብሔር ያላዘዘውን በመናገሩ ሞትን አስከተለ። Yossi Feintuch. The Folly of Impetus Speech: Four Biblical Incidents. Jewish Bible Quarterly. Vol. 34 No. 1, 2006. ገጽ 16-19

16የግርጌ ማስታወሻ 14ን ይመልከቱ።

No comments:

Post a Comment